የወራቤ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ ካውንስል አባላት በስልጤ ዞን ሚቶ ወረዳ የተካሄደው በማህበረሰብ ተሳታፊነት ላይ የተመሰረተ የሀገር በቀል የፍየሎች ዝሪያ ማሻሻያ ፕሮግራም የስራ ግምገማ አካሄዱ

News news
2026-11-07 11:07:33

የዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ሽግግር  እና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መምህር ጀማል ሬድዋን በዛሬው ዕለት የተደረገው የጉብኝት ግምገማ በወረዳው የሚገኙ የሀገር በቀል የፍየሎች ዝሪያ ማሻሻያ ማህበር የተደራጁ አርሶአደሮችን አጠቃላይ ያሉበትን የስራ ሒደት እና እስካሁን ያስገኙዋቸውን ውጤቶችን ምልከታ ለማድረግ የተደረገ ፕሮግራም እንደሆነ አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቱን ከመሰረተ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እንዲሁም ክትትሎችን እያደረገ እንደሚገኝ እና  የማህበሩ አባላትም ያላቸው ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ  በየጊዜው ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል ።

የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን መምህር አላሙዲን ቁፋ በበኩላቸው በማህበሩ እየታዩ ያሉ ለውጦች ቀጣይነት እንዲኖራቸው የማህበሩ አባላት ከወዲሁ እራሳቸውን በቁጠባ እንዲሁም መረጃዎችን በአግባቡ እና በሰዓቱ ማድረስ ላይ ተጠናክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ፕሮጀክቱ የበለጠ ምርታማነት እና የአርሶ አደሮችን ውጤታማነት እና የኑሮ መሻሻልን ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲው ክትትል እና ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በስልጤ ዞን ግብርና ልማት መምሪያ  የእንስሳት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሁሴን ሹክራላ ወራቤ ዩኒቨርሲቲ በወረዳው ምርጥ የፍየል ዝሪያን ለሀገር ብሎም ለአለም ለማስተዋወቅ እና ለማዳረስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆኑንና ይህን ተግባር ለማሳደግ እንዲሁም ለማስቀጠል ዞኑና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

የማህበሩ አባላት ወራቤ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቡን መሰረት ያደረገ የሀገር ውስጥ የፍየል ዝሪያ ማሻሻያ ፕሮጀክት በወረዳቻው ከመሰረት ጀምሮ በኑራቸው እንዲሁም በፍየል ዝሪያ ማሻሻል ላይ ያላቸው ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን በመግለፅ ዩኒቨርሲቲው ላደረገላቸው መልካም ተግባር አመስግነዋል።

 በስራ ግምገማ ጉብኝት የዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር እና የግብርና ኮሌጅ ካውንስል አባላት የዞን ፣ የወረዳ ጽ/ቤት አመራሮች እና የማህበሩ አባላት ተሳትፈዋል።

 

ዕውቀት ለልህቀት

ወራቤ ዩኒቨርሲቲ

2-878256.jpg 3-577603.jpg 4-248584.jpg